Ezekiel 18

ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ ትሞታለች

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“ስለ እስራኤል ምድር፣

“ ‘አባቶች ጐምዛዛ የወይን ፍሬ በሉ፤
የልጆችንም ጥርስ አጠረሰ’
እያላችሁ የምትመስሉት ተምሳሌት ምን ለማለት ነው?

3“በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ልዑል እግዚአብሔር፤ ከእንግዲህ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ምድር አትመስሉም። 4እነሆ ነፍስ ሁሉ የእኔ ናት፤ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች ሁሉ የልጁም ነፍስ የእኔ ናት፤ ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች።

5“በቅንነትና በትክክል የሚሠራ፣
ጻድቅ ሰው ቢገኝ፣
6በኰረብታ ባሉ አብያተ ጣዖት የቀረበውን አይበላም፤
በእስራኤል ቤት ወዳሉት ጣዖታት አይመለከትም
የባልንጀራውን ሚስት አያባልግም፤
ከሴት ጋር በወር አበባዋ ጊዜ አይተኛም።
7ማንንም አይጨቍንም፤
ነገር ግን በመያዣ የወሰደውን እንኳ ለተበዳሪው ይመልሳል፤
ለተራበ የራሱን እንጀራ፣
ለተራቈተም ልብስ ይሰጣል እንጂ፣
በጕልበት አይቀማም።
8በዐራጣ አያበድርም፣
ከፍተኛ ወለድም አይቀበልም
ወይም ወለድ አይወስድም፤ እንዲሁም በ13 እና 17

እጁን ከበደል ይሰበስባል፤
በሰውና በሰው መካከል በትክክል ይፈርዳል።
9ሥርዐቴን ይከተላል፤
ሕጌንም በቅንነት ይጠብቃል።
ይህ ሰው ጻድቅ ነው፤
ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል፤
ይላል ጌታ እግዚአብሔር
10“ነገር ግን ይህ ሰው ደም የሚያፈስ ወይም ከሚከተሉት ኀጢአቶች ማንኛውንም
ወይም ማናቸውንም በወንድሙ ላይ
የሚፈጽም ዐመፀኛ ልጅ ቢኖረው፣
11አባትየው አንዱንም ባያደርግ፣

“ልጁ ግን በኰረብታ መስገጃ የቀረበውን ቢበላ፣
የባልንጀራውን ሚስት ቢያባልግ፣
12ድኻውንና ችግረኛውን ቢጨቍን፣
በጕልበት ቢቀማ፣
በመያዣነት የወሰደውን ባይመልስ፣
ወደ ጣዖታት ቢመለከት፣
አስጸያፊ ተግባራትን ቢፈጽም፣
13በዐራጣ ቢያበድር፤ ከፍተኛ ወለድም ቢቀበል፣
እንዲህ ዐይነቱ ሰው በሕይወት ይኖራልን? ከቶ አይኖርም! እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች አድርጓልና በርግጥ ይሞታል፤ ደሙም በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል።

14“ይህም ልጅ ደግሞ በተራው ልጅ ቢወልድና ልጁም አባቱ ያደረገውን ኀጢአት ሁሉ አይቶ ባይፈጽም፣ ይኸውም፦

15“በኰረብታ መስገጃ የቀረበውን ባይበላ፣
በእስራኤል ቤት ወዳሉት ጣዖታት ባይመለከት፣
የባልንጀራውን ሚስት ባያባልግ፣
16ሰውን ባይጨቍን፣
ብድር ለመስጠት መያዣ ባይጠይቅ፣
በጕልበቱ ባይቀማ፣
ነገር ግን ምግቡን ለተራበ፣
ልብሱን ለተራቈተ ቢሰጥ፣
17እጁን ደኻን ከመበደል ቢሰበስብ፣
ዐራጣ ወይም ከፍተኛ ወለድ ባይቀበል፣
ሕጌን ቢጠብቅ፣ ሥርዐቴንም ቢከተል፣
በሕይወት ይኖራል እንጂ በአባቱ ኀጢአት አይሞትም።
18አባቱ ግን የሰውን መብት ስለ ደፈረ፣ ወንድሙን በጕልበት ስለ ቀማና በሕዝቡ መካከል የማይገባውን ስላደረገ በገዛ ኀጢአቱ ይሞታል።

19“እናንተ ግን፣ ‘ልጅ ስለ አባቱ ኀጢአት ለምን አይቀጣም?’ ትላላችሁ። ልጁ ቀናና ትክክለኛውን ነገር ስላደረገ፣ ሥርዐቴንም ሁሉ በጥንቃቄ ስለ ጠበቀ በሕይወት ይኖራል። 20መሞት የሚገባት ኀጢአት የሠራችው ነፍስ ናት። ልጅ በአባቱ ኀጢአት አይቀጣም፤ አባትም በልጁ ኀጢአት አይቀጣም። ጻድቁ የጽድቁን ፍሬ ያገኛል፤ ኀጢአተኛውም የኀጢአቱን ዋጋ ይቀበላል።

21“ኀጢአተኛ ከሠራው ኀጢአት ሁሉ ተመልሶ ሥርዐቴን ሁሉ ቢጠብቅ፣ ቀናና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 22በደሉ ሁሉ አይታሰብበትም፤ በጽድቅ መንገድ ሄዷልና በሕይወት ይኖራል። 23በውኑ ኀጢአተኛ ሲሞት ደስ ይለኛልን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ይልቁን ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ሲኖር ደስ አይለኝምን?

24“ጻድቅ ሰው ግን ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ፣ ኀጢአተኛው የሚያደርገውንም አስጸያፊ ነገር ቢፈጽም፤ ይህ ሰው በውኑ በሕይወት ይኖራልን? ከሠራው ጽድቅ አንዱም አይታሰብለትም፤ ታማኝ ባለመሆኑና ከፈጸመው ኀጢአት የተነሣ ይሞታል።

25“እናንተ ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስማ፤ መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነውስ የእናንተ መንገድ አይደለምን? 26ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ በኀጢአቱ ይሞታል፤ ከፈጸመውም በደል የተነሣ በሕይወት አይኖርም። 27ኀጢአተኛው ግን ከክፉ ሥራው ተመልሶ በታማኝነትና በቅንነት ቢኖር ሕይወቱን ያድናል። 28የፈጸመውን በደል ሁሉ ተገንዝቦ ካደረገው ክፋት ሁሉ ስለ ተመለሰ፣ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 29የእስራኤል ቤት ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ! መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነችውስ የእናንተ መንገድ አይደለችምን?

30“የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለዚህ እንደየሥራችሁ በእያንዳንዳችሁ ላይ እፈርዳለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንግዲህ ንስሓ ግቡ በኀጢአት እንዳትጠፉ፣ ከኀጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ። 31በእኔ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ ወደ ኋላ ጣሉት፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ? 32ማንም እንዲሞት አልሻምና፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ወደ እኔ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ!

Copyright information for AmhNASV